በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም

“ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።”የዮሐንስ ወንጌል 3:14-18

“ሥራህን አውቃለሁ” ራእ 2:19

ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ። ራእ2:19

ጥንታዊት፤ታሪካዊት፤ ብሔራዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተሰጣት መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን መሠረት ከውስጥና ከውጭ የሚነሱባትን የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ፈተናዎች በመቋቋም ዘመናትን የተሻገረችና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ለትውልድ የሚተላለፉ በርካታ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ሥራዎችን በመሥራት ሃይማኖትን፤ታሪክንና ባሕልን ጠብቃ ያቆየች መሆኗን ማንም የሚመሰክረው ሐቅ ነው።በአለት ላይ የተመሠረተችው ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እምነቷን፤ ክብሯንና ታሪኳን በሚገባ ጠብቃ ለትውልድ ለማስተላለፍ የቻለችው በቀደምት ወላጆቻችን አንድነት፤ጽኑዕ እምነት፤ ጥንካሬና አርቆ አሳቢነት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

ክርስትና በእምነት እያደጉ እና እየጠነከሩ የሚጓዙበት የሕይወት መንገድ ነው። ስለሆነም  በእምነት ጸንቶ ለመገኘትና እስከ ሞት ድረስ ለመታመን የግድ በእምነት አድጎና ጠንክሮ መገኘት ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ነው። ሥነ ምግባር መለት መልካም ጠባይና በጎ ሥራ በመሥራት የሚገለጥ ሲሆን ክርስቲያናዊ የሚለወ ቃል ሲጨመርበት ይተለይና የተሟላ መገለጫ እንዲሆን  ይድወርገዋል። መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ምንጊዜም የማይለወጥና ይተሟላ ሆኖ ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ጸንቶ ከኖረ ብቻ  መሆኑ አያጠያይቅም። ከጥንት ዘመን ጀምሮ በእምነታቸው ጠንካሮች የነበሩ ሰዎች በጉዟቸው ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኙት ተመስክሮላቸዋል። እግዚአብሔር ደስ የተሰኘባቸው የእምነት አርበኞች በእምነታቸው ጥንካሬ በጎ ሥራ በመሥራትና ዓለምን ድል በማድረግ በሕይወት ዘመናቸው የእግዚአብሔርን ሕያውነት፤ ድል አንድራጊነትና ኃያልነት በሕይወት ዘመናቸው የመሰከሩ መሆናቸውን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያውን መልእክቱ  መስክሮላቸዋል። ዕብ 11:1-30

በየእለቱ የመንፈስን ፍሬ የሚያፈራ ክርስቲያን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን የተተከለ ቅጠሉ የማይጠወልግ ልምላሜና ፍሬ የማይለየው የሃይማኖት ተክል ሲሆን በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው በክፉዎች ምከር አይሄድም፤ በኃጢአተኞችም መንገድ አይቆምም፡ በዋዘኞች ወንበር አይቀመጥም። ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቀመጡም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ስለሚለው ሕጉን በቀንና በሌሊት በማሰብና እንደ እግዚአብሔር ሕግ ትእዛዝ መሠረት ጸንቶ ይኖራል ።መዝ1:1-6

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሲባል የሰው ልጅ ምድራዊውን በሰማያዊ ጊዜያዊውን በዘለአለማዊ፤ የሚታየውን በማይታየውና በማይዳሰሰው የሚለውጥበትና ለሰማያዊ መንግሥት የሚበቃበት ሕይወት ነው። በመሆኑም የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ዋና መለኪይያው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት  ማደግና  ፍሬ ማፍራት  የሚችል ሕይወት ያለው ሲሆን ብቻ ነው።

“ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።” ፊልጵ1:9-11

ስለሆነም አንድ ሰው በሰው ፊት ሲትያ በውጭ የሚታየው ሕይወቱና ሥራው የሚያስደስትና እንከን የማይወጣለት ልሆን ይችላል። የእግዚአብሔር ቃል በውስጡ ከሌለ ግን በእግዚአብሔር ሚዛን ተመዝኖ ማለፍ እንደማይችል ቅዱስ ያዕቆብ ከጻፈው በመልእክት መረዳት ይቻላል።ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። ያዕ1:22-25

በአንጻሩ ደግሞ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ቃል እየራቀ ግብሩም ወድ እንስሳት ጠባይ እየተለወጠ ሲሄድ የሚወቅሰው  ሕሊና ሊኖረው ስለማይችል ክቡር ሆኖ የተፈጠረበት አዳማዊ ባሕርይ ፈጽሞ እንደሚለወጥ ከናቡከደነፆር የሕይወት ታሪክ በአጭሩ መረዳት ይቻላል።”በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።” ዳን4:33

ክርስትና ሕያው ተስፋና ፍጽም የሆነ ሰማያዊ በረከት የአለበት እመንት እንደሆነ በግልጥ ይታወቃል። ነገር ግን የዚህ ፍጹም ተስፋ ባለቤትና የበረከቱ ተሳታፊ መሆን የሚቻለው ክርስትና የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል በመዘጋጀት እንጂ እንዲሁ በስሙ በመጠራት ብቻ አይደለም። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በመከራና በልዩ ልዩ ፈተና ውስጥ ጨክኖ ማለፍ ክርስትና ክርስትናነቱ የሚታወቅበት ዋና መለያ ምልክት ነው። “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤”ፊል 1:29

በየዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች እምነታቸው ያስጨበጣቸውን እጅግ የከበረ ነገር ሁሉ እስከ መጨረሻው ይዘው ለመጓዝ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በእመንት ጉዞአቸው ሊያሰናክላቸው ከተደቀነው ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ በድል ለማለፍ “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” እራ 2:10  ተብሎ በተጻፈው ቃል መሠረት የደም ዋጋ በመክፈልና ሕይወታቸውን የተወደደ መስ ዋእት በማድረግ ከባድ ተጋድሎ ፈጽመው አልፈዋል። ምድራዊ ተድላና ደስታ ዘለዓለማዊ የሆነው ሰማያዊ ሐሴት ፈጽሞ ሊተካ ስለማይችል በሚታየውና በሚዳሰሰው ጊዜአዊ ምኞት ሳይታለሉ እምነታቸው የጠየቀውን ታላቅ ዋጋ  በእምነት ተቀብለዋል ሮሜ 8:17። ይህ እውነት በቀደሙት የእምነት አርበኞች ቅዱሳን ነቢያትና ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሕይወት የተፈጸመ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ  በዕብ 11፡24 በሰፊው  በማተት ዘግቦታል።  ይህም የሚያስረዳው አንድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር እንዲሁ የተቀበለውን የዘለዓለም ድኅነት እንዲት መያዝ እንደአለበትና በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚመላለሱ የእምነት አረባኛ በመባል የሚታወቁ ሰዎች  በሥጋ ዘመናቸው የደረሰባቸው ቀላል አለመሆኑን ነው።

በዚህ ዓይነት  አንድ ክርስቲያን ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ በማስገዛት በእመነት የጠነከረና ከማናቸውም ነገር ይልቅ መንግሥቱንና ጽድቁን በማስቀደም በእምነት ለማደግ ጥረትና ትጋት ሲታይበት ብቻ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ። እነዚህ ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና” በማለት የአዋጅ ጥሪ ያቀርባል። 2ጴጥ1:10

በዚህ ቅዱስ ቃል መሠረት ክርስቲያኖች እስከ መጨረሻው ዕለት ድረስ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሰጣቸውን የዘለዓለም ድኅነትና ሕይወት አስጽንተው መያዝ ግዴታ እንዳለባቸውና ከእምነታቸው እንዳይሰናከሉ የሕይወት መስዋእትነትን ሊያስከፍል እስከሚችል ድረስ እንኳ ትጋትን፤ ጽናትንና ትእግስትን  በመያዝ በእምነት መጠንከርና መጎልመስ እንዳለባቸው የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል። ማር 13:13

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።

አባ ቴዎፍሎስ